2 Chronicles 21

1ኢዮሣፍጥ እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮሆራምም በእርሱ ፈንታ ነገሠ። 2የኢዮሆራም ወንድሞች የሆኑት የኢዮሣፍጥ ልጆችም ዓዛርያስ፣ ይሒኤል፣ ዘካርያስ፣ ዔዛርያስ፣ ሚካኤልና ሰፋጥያስ ይባላሉ። እነዚህ ሁሉ የእስራኤል
በሁለተኛው የዜና መዋዕል መጽሐፍ ተደጋግሞ እንደ ተጠቀሰው ይህ ይሁዳ ነው።
ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ።
3አባታቸውም ብዙ የብርና የወርቅ፣ የውድ ዕቃዎችም ስጦታ እንዲሁም በይሁዳ ያሉትን የተመሸጉ ከተሞች ሰጣቸው፤ ነገር ግን መንግሥቱን ለኢዮሆራም ሰጠ፤ የበኵር ልጁ ነበርና።

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሆራም

21፥5-10፡20 ተጓ ምብ – 2ነገ 8፥16-24 4ኢዮሆራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ ከተቀመጠ በኋላ፣ ወንድሞቹን በሙሉ ከጥቂት የእስራኤል አለቆች ጋር በሰይፍ ገደለ።

5ኢዮሆራም በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሰላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ። 6እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንደ አደረገው ሁሉ፣ የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 7ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ካደረገው ኪዳን የተነሣ፣ የዳዊትን ቤት ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም የሚጸና መብራት እንዲኖር ለማድረግ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

8በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ፣ የራሱን ንጉሥ አነገሠ። 9ስለዚህ ኢዮሆራም የጦር ሹማምቱና ሠረገላዎቹን ሁሉ ይዞ ወደዚያው ሄደ። ኤዶማውያንም እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ሁሉ ከበቡ፤ እርሱ ግን በሌሊት ተነሥቶ የከበቧቸውን መታ። 10ኤዶምም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንደ ዐመፀ ነው።

ኢዮሆራም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የልብና ከተማ በዚያኑ ጊዜ ዐመፀችበት።

11ከዚህም በላይ በይሁዳ ኰረብቶች ላይ መስገጃ ስፍራዎች ሠርቶ የኢየሩሳሌም ሕዝብ በዚያ እንዲያመነዝር አደረገ፤ ይሁዳንም አሳተ።

12ከነቢዩ ከኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢዮራም መጣ፤

“የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አንተ በአባትህ በኢዮሣፍጥ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህም፤
13ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደሃል፤ የአክዓብ ቤት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲያመነዝር እንዳደረገ ሁሉ፣ አንተም ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲያመነዝሩ አሳሳትሃቸው፤ እንዲሁም ካንተ የሚሻሉትን፣ የገዛ ወንድሞችህንና የአባትህን ቤተ ሰብ አባላት ገደልሃቸው፤ 14ስለዚህ እነሆ፤ እግዚአብሔር ሕዝብህን፣ ልጆችህን፣ ሚስቶችህንና ያለህን ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይመታል። 15አንተም ራስህ በየዕለቱ እየባሰ በሚሄድ የአንጀት በሽታ ክፉኛ ትታመማለህ፤ በመጨረሻም ሕመሙ አንጀትህን ወደ ውጭ ያወጣዋል።’ ”

16 እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩ ዐረቦችን በኢዮሆራም ላይ በጠላትነት እንዲነሡ አደረገ። 17እነርሱም በይሁዳ ላይ ወጡ፤ ወረሯትም። በንጉሡ ቤተ መንግሥት የሚገኘውን ዕቃ ሁሉ፣ ከወንዶች ልጆቹና ከሚስቶቹ ጋር ወሰዱ፤ ከመጨረሻ ልጁ ከአካዝያስ
በዕብራይስጥ አካዝ እና ኢዮአስ አንድ ናቸው።
በስተቀር አንድም ልጅ አልቀረለትም።

18ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር ሊድን በማይችል የአንጀት በሽታ ኢዮሆራምን ቀሠፈው። 19ሕመሙም ሲያሠቃየው ከቈየ በኋላ፣ በሁለተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ በዚሁ ሳቢያ አንጀቱ ወጥቶ በከባድ ሥቃይ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ክብር እሳት ያነድዱ ነበር፤ ለእርሱ ግን አላነደዱለትም።

20ኢዮሆራም ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ። በሞተ ጊዜም ማንም አላዘነለትም፤ በዳዊትም ከተማ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልቀበሩትም።

Copyright information for AmhNASV